የጦር ኃይሎች ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ለማሻሻል ያከናወነው ተጨማሪ የህክምና መስጫ ግንባታ በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀንአ ያደታ ተመርቆ በይፋ ተከፈተ።

[#if smallImage??]
    [#if smallImage?is_hash]
        [#if smallImage.alt??]
            ${smallImage.alt}
        [/#if]
    [/#if]
[/#if]
ሰኔ 4 ቀን 2013
የጦር ኃይሎች ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ለማሻሻል ያከናወነው ተጨማሪ የህክምና መስጫ ግንባታ በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀንአ ያደታ ተመርቆ በይፋ ተከፈተ።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀንአ ያደታ ሆስፒታሉ ለዘመናት የነበሩበትን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ከጀመራቸው ስራዎች መሀከል የገነባቸውን ባለ ሁለት ፎቅ የእናቶችና ህፃናት ህክምና መስጫ ህንፃና የኤም አር አይ ምርመራ ማድረጊያ ግንባታዎች መርቀው ከከፈቱ በኋላ እድሳት የተደረገለትን የራዲዮሎጂ አገልግሎት መስጫ ክፍልና ሌሎች የተከናወኑ ተግባራትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የጦር ኃይሎች ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የለውጥ ሂደቱ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም አደረጃጀቱን እንደ አዲስ ከማስተካከል አንስቶ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት በመስጠት የስልጠናና የምርምር ስራዎችን በተገቢው እንዲያከናውን በተቋም ደረጃ ትኩረት የተሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውን ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነአ ያደታ በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ ገልፀዋል ።
ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነአ ያደታ አያይዘውም ሆስፒታሉ አገልግሎቱን ለማሻሻልና ለማዘመን ባከናወናቸውና በህግ ማስከበር ዘመቻው ላስመዘገባቸው አበረታች ውጤቶች ሀላፊነታቸውንና ሙያዊ ግዴታቸውን በብቃት ለተወጡና ለሆስፒታሉ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል ።
ሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት አሰጣጡን ምቹ ፣ ቀልጣፋ ፣ተደራሽ እና ጥራት ያለው እንዲሆን በዘመናዊ መገልገያ መሣሪያዎች እያጠናከረ እንደሚገኝም የሆስፒታሉ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ዶክተር ሀይሉ እንዳሻው በስነስርአቱ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት ገልፀዋል።
የጦር ኃይሎች ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሰራዊቱ፣ ለሰራዊቱ ቤተሰቦች ፣በክብርና በጡረታ ለተሰናበቱ የሰራዊት አባላትና ለከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የሚሰጠው የህክምና አገልግሎትም በሚጠበቅበት ልክ እንዲሆን የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
የጦር ኃይሎች ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቀደም ባሉት ጊዜያት ወደ ሌሎች የህክምና ተቋማት እየላከ ያሰራቸው የነበሩ የተለያዩ ከፍተኛ የምርመራ ውጤቶችን በማስቀረት እስከ 95 በመቶ የሚደርሱ የምርመራ አይነቶችን በራሱ መርምሮ ውጤት ማወቅ የሚያስችሉትን ዘመናዊ መሳሪያዎች በዚህ አመት ብቻ ከ124 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ገዝቶ ወደስራ አስገብቷል።
የሆስፒታሉን ታሪካዊ ዝና ለመመለስ ፣ ያለውን ረጅም እድሜ ያህል እየተሻሻለ ፣ እያደገና እየዘመነ እንዲሄድ ለማድረግና የመከላከያ ከፍተኛ የህክምና ማዕከል የመሆን ራዕዩን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ አዛዡ ብርጋዲየር ጄኔራል ዶክተር ሀይሉ እንደሻው ጥሪ አቅርበዋል።
ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ የህግ ማስከበር ዘመቻውን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት ከሆስፒታሉ ጎን በመቆም የየራሳቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱ የፌዴራል ተቋማት ፣ ለተለያዩ መንግስታዊና የግል ማዕከላት እንዲሁም ለሆስፒታሉ ጠንካራ ሙያተኞችና ሰራተኞች ምስጋና በማቅረብ ሽልማትና የእውቅና የምስክር ወረቀት ሰጥቷል።
ሳሙኤል ወንድሙ
ፎቶግራፍ ብርቱካን ረጋሳ